Wednesday, 4 May 2016

ከፆም ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች

No comments:

ከፆም ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች

1.ፆመኛ ትጥበትን ግዴታ የሚያደርግ (ጀናባ) ላይ ሆኖ ፆምን ማቀድ (መነየት) ከዚያም ጐህ ከቀደደ በኋላ መታጠብ ይፈቀድለታል፡፡

2.
በረመዳን ወር በወሊድ እና በወር አበባ ደም ላይ ያሉ ጐህ ከመቅደዱ በፊት ከደሙ ከጠሩ ከዚያ በኋላ ቢታጠቡም እንኳ መፆም ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ 

3.
ፆመኛ ጥርሱን መነቀል፣ ቁስሉን መታከም እና በዓይኑ ወይም በጆሮው በኩል የሚወሰዱ በጠብታ መልክ የተዘጋጁ መድሃኒቶችን መጠቀም ይፈቀድለታል፡፡ ይህንን በማድረጉም ጐሮሮው ውሰጥ የጠብታው ጣዕም ቢታወቀው እንኳ ፆሙ አይበላሽም፡፡

4.
በቀኑ መጀመሪያም ይሁን መጨረሻ ክፍለ ጊዜ መፋቂያን መጠቀም ፆመኛ ላልሆኑ ሰዎች ሱና እንደሆነው ሁሉ ለፆመኛም የተወደደና የተፈቀደ ነው፡፡

5.
ፆመኛ ከከፍተኛ ሙቀትና የውሃ ጥም ራሱን ለማ ስታገስ ውሃ በራሱ ላይ ማፍሰስም ይሁን መታጠብ እንዲሁም የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያዎችን መጠቀም ይፈቀድለታል::

6.
ፆመኛ መታፈንን ሊያስከትሉ የሚችሉ (እንደ አስም) ባሉ በሽታዎች የተነሳ የሚከሰት የአየር እጥረትን ለመከላከል ሲባል በአፍ የሚሳቡ (የአየር እጥረት መከላከያ) መድሃኒቶችን መጠቀም ይፈቀድለታል፡፡

7.
ፆመኛ ሰው ከንፈሮቹ እና አፉ ቢደርቁ በውሃ ማራስ ቢፈቀድለትም ውሃን በጐሮሮው ውስጥ ከማመላለስ ግን ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡

8.
ፆመኛ ጐህ ሊቀድ (ለፈጅር) ጥቂት ጊዜ እስኪቀረው በለሊት የሚመገበውን ምግብ (ሰሁር) ማዘግየት፣ ፀሀይ ከጠለቀችም ፆም መፍታትን (ማፍጠርን) ማቻኰል ይወደድለታል። እንዲሁም የተምር እሸት ካላገኘ በሌላ የተምር አይነት፤ ካልሆነም በውሃ ወይም ከተፈቀዱ የምግብ አይነቶች በማንኛውም ምግብ ማፍጠሩ ካላገኘም ማፍጠሪያ እስኪያገኝ በልቡ ማፍጠርን ማሰቡ ሱና ይሆንለታል፡፡

9.
ፆመኛ በበጐ ፍቃደኝነት የሚፈፀሙ ሰናይ ተግባራትን ሊያበዛና የተከለከሉ ነገሮችን በሙሉ ሊርቅ ይገባል፡፡

10.
ፆመኛ ግዴታ የሆኑ ተግባራትን ማዘውተር፣ ከተከለከሉ (ሐራም) ነገሮች ሁሉ መራቅ፣(የጀመዓ ሰላት የሚመለከተው ከሆነ) የአምስት ወቅት ሰላቶችን ጊዜያቸውን ጠብቆ በጀመዓ መስገድ፣ ውሸትን፣ ሐሜትን፣ ማታለልን፣ ከወለድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎችን እንዲሁም ማንኛውም የተከለከለ ንግግርና ተግባርን መተው ግዴታ ይሆንበታል፡፡

No comments:

Post a Comment

 
back to top