Wednesday, 4 May 2016

ሰዎች ከፆም አንፃር

No comments:

ሰዎች ከፆም አንፃር

ፆም በእያንዳንዱ ለአካለ መጠን በደረሰ፣ የጤናማ አዕምሮ ባለቤት፣ መፆም የሚያስችለው ጤና ያለው እና መንገደኛ ባልሆነ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፡፡

ሙስሊም ያልሆነ ሰው የፆም ግዴታነት በቀጥታ አይመለከተውም፡፡ ቢሰልምም ከመስለሙ በፊት ያለፈውን ፆም የመክፈል (ቀዳእ የማውጣት) ግዴታ አይኖርበትም፡፡

ለአካለ መጠን ያልደረሰ (ህፃን) ፆም ግዴታ አይሆንበትም ነገር ግን እንዲለምደው በማሰብ እንዲፆም ይታዘዛል፡፡

የአዕምሮ በሽተኛ የረመዳንን ወር መፆምም ሆነ ለፆም ማካካሻ የሚሆን ፆም (ምስኪን ማብላት) ግዴታ አይሆንበትም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ነገሮ ችን መለየት የተሳነው ዘገምተኛ ሰው እና የጃጀ ሽማግሌ ፆም ግዴታ አይሆንባቸውም፡፡

እንደ እርጅናና ለመዳን ተስፋ እንደሌለው በሽታ ባሉ ዘውታሪ ምክንያቶች የተነሳ መፆም የተሳነው ሰው ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ምስኪን ያበላል፡፡

መዳኑን ተስፋ በሚያደርገው (ጊዜያዊ በሽታ) የተያዘ ሰው መፆም ከከበደው ከበሽታው ሲያገግም በመፆም ያካክሳል፡፡

በእርግዝናና በማጥባት ላይ ያሉ በዚሁ ምክንያት ፆም ከከበዳቸው አሊያም በልጆቻቸው ላይ ጉዳት እንዳይከሰት ከሰጉ ፆምን በመፍታት ስጋቱ በተወ ገደና በገራላቸው ወቅት ይፆማሉ፡፡

በወር አበባና በወሊድ ደም ላይ ያሉ (በዚህ ወቅት) የማይፆሙ ሲሆን ያለፏቸውን የፆም ቀናት በሌላ ጊዜ በመፆም ያካክሳሉ፡፡

በእሳት ቃጠሎ አሊያም በውሃ የመስጠም (ወይም በተመሳሳይ) አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመታደግ የነፍስ አድን ስራ ላይ በመሰማራቱ ፆም ለመፍታት የተገደደ ሰው ፆሙን ፈትቶ በሌላ ጊዜ በመፆም ያካክሳል፡፡

መንገደኛ (ሙሳፊር) ሰው ከፈለገ ይፆማል ከፈለገም ፆሙን በመፍታት በሌላ ጊዜ ያካክሳል፡፡ ይህም ማለት (በዘውታሪነት ሳይሆን) በድንገት እንደ ዑምራ ላሉ ተግባራት የሚጓዘውንም ይሁን በዘውታሪነት ጉዞ ላይ የሚሆኑትን (የአገር አቋራጭ) ሕዝብ ማመላሻ ሠራተኞችን ይመለከታል፡፡ እነዚህ ሰዎች በመኖሪያ አገራቸው እስካልሆኑ ድረ ከፈለጉ ፆምን በመፍታት በሌላ ጊዜ ያካክሳሉ፡፡



No comments:

Post a Comment

 
back to top